የድሬ ዳዋ ፖሊስ አመራሮችና አባላት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በለውጡ የተፈጠሩ አቅሞችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ) የድሬዳዋ ፖሊስ ከፍተኛ አመራርና አባላት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በለውጡ የተፈጠሩ አቅሞችን ተዘዋውረው ጎበኙ።
ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የድሬዳዋ ፖሊስ ከፍተኛ አመራርና አባላትን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው የድሬዳዋ ፖሊስ ከለውጡ በፊት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረ ተቋም መሆኑን በማስታወስ በለውጡ በተሰራው ሪፎርም ከመፍረስ በመታደግ አሁን ላይ በሞዴልነት ለመታየት የበቃ እና ለሀገራችን የፖሊስ ተቋማት እንደምሳሌ የሚጠቀስ ፕሮፌሽናል የፖሊስ አቅም እየገነባ እንዳለ ገልፀው በዚህም ድሬዳዋ ከተማም ተመራጭ የሰላም ከተማ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተጠሪ በመሆኑ ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆንና የተገኙ ውጤቶችም ቀጣይነት እንዲኖራቸው የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎች እና የሎጅስቲክ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ገልፀዋል፡፡
ከፍተኛ አመራርና አባላት በጉብኝታቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማዕከል፤ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ፣ የሎጂስቲክ ዋና መምሪያ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል፣ የፖሊስ ጀግኖች ማዕከልን፣ በቅርቡ ታድሶ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የፖሊስ መኮንኖች ክበብ እና ሌሎች በለውጡ የተፈጠሩ አቅሞችን ጎብኝተዋል፡፡