የኮሚሽነር ጄኔራል መልዕክት

photo_2022-03-30_17-55-54 (2)_1650961997.jpg

የክቡር ኮሚሽነር ጀነራል መልዕክት

የተከበራችሁ ውድ የሀገራችን ህዝቦች፣ የተከበራችሁ መላው የሃገራችን ፖሊሶችና አጋር የፀጥታ አካላት፣ የተከበራችሁ መላው የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች። ይህንን ለውጥ ከግብ ለማድረስና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብሎም ዜጎች ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲመሩ ማስቻል ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በህግ የተሰጠውን ወንጀልን በመከላከል የህብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ህገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ ከምን ጊዜውም በላይ በቂ ዝግጅት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን የሕዝብን ደህንነት ማስከበር የኮሚሽኑ ዋነኛ ተግባር መሆኑ ይታወቃል። ይህን ተግባር ከግብ ለማድረስ ኮሚሽኑ ከሀገራችን ህዝቦች ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ ነው።

ከኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሠረታዊ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የሆነው በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ የመገንባት ዓላማ ከግብ የሚደርሰው የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበራቸው ሲረጋገጥ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች አቅደው ግጭቶችን በመቀስቀስ ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሱ የሚገኙ አካላትን የሕግ የበላይነትና የህዝባችንን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል ኮሚሽኑ ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ እነዚህን መብቶችና ነፃነቶች በማስከበርና በማክበር ድርሻውን ይወጣል።

ኮሚሽኑ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት በጥናትና ምርምር፣ ከአዝማሚያ ትንተና እና ከህዝብ አስተያየት በመነሳት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በማምከን የቅድመ መከላከል ስራ ይሰራል። ከዚህ አልፎ ወንጀል ከተፈፀመ የወንጀል ድርጊቱን በማጣራት ማስረጃ በማሰባሰብ በጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከአቃቤ ህግ አካላት ጋር በመተባበር እስከ መጨረሻው ጉዳዩን በመከታተል ፍርድ እንዲሰጥ ያደርጋል።

በህዝባችን ትግልና ግፊት የመጣው ለውጥ ሀገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር፣ ለሀገራችን ዘላቂ ብልጽግና መሠረት የሚጥል፣ የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና ህዝባችን በኮሚሽኑ ላይ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት የማይቋረጥ ቋሚ የአሰራር ሥርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ  ላይ እንገኛለን።

በቀጣይም ኮሚሽኑ ከህዝባችንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኢኮኖሚ አሻጥር ፣ ሙስናንና ሌብነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወዘተ. ላይ የተሳተፉ ህገ ወጦችን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ኮሚሽኑ የሀገራችንን ህግና ስርዓት በማያከብሩና ጥፋት የሚፈጽሙ አካላትን የማይታገስና ለድርድር የማያቀርብ ይሆናል።

ለኮሚሽኑ በህገ-መንግስቱና በሌሎች ህጎች ተለይተው የተሰጡትን፤ ዝርዝር ተልዕኮዎችና ተግባራት መላው ህዝባችንን በማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት (Community Policing) መርህ ከጎናችን አሰልፈን ሙስናና፤ ሌብነት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀም እየተዋጋን፣ ዘመናዊ ፖሊሳዊ እውቀትና ክህሎት የሚያስጨብጡንን ልምዶችና ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማሳደግ፣ በመልካም ሙያዊ ዲስኘሊንና ስነምግባር ታንጸን ተልዕኮዎቻችንን በብቃት እንወጣለን።

ወንጀልን በመከላከልና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ተልዕኮዎቻችንን ለመወጣት በምናደርገው ጥረት የሀገራችን ህዝቦች ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ ፖሊስና ኅብረተሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ሁሉ ከኛ የሚጠበቀውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ጠንክረን እንደምንሠራ ያለኝን ፅኑ እምነት ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡  

በመጨረሻም ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ ዘንድ ለመድረስ የሁለትዮሽ ተግባቦት ዘዴ /Two way communication/ በመጠቀም በየጊዜው የሚወስዳቸው ህጋዊ እርምጃዎችንና ሌሎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በቀጣይነት ለህዝባችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ዌብሳይት ሥራ መጀመሩን እያበሰርኩ በዚህ ዌብሳይት በስራችን ላይ ያላችሁን ማንኛውንም አስተያየትና ጥቆማ በማድረስ መረጃን በቀጣይነት እንደምንለዋወጥ ተስፋ አደርጋለሁ። አመሰግናለሁ፡፡ መልካም የስራ ጊዜ ይሁንልን።