የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና አባላት በአረንጓዴ አሻራ ቀን ተሳትፎ አደረጉ

        በመላ አገሪቱ 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል የተያዘዉን መርሐ ግብር ተከትሎ 12617 የሚደርሱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና አባላት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 186,077 ችግኝ በመትከል  የሀገሪቱን ሰላም እና ፀጥታ ከመጠበቅ ተልእኳቸዉ ጎን ለጎን ችግኞችን በመትከል በሀገሪቱ የሚከናወነዉን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የበኩላቸዉን ድርሻ መወጣታቸዉ ታዉቋል፡፡

       በኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን የአስተዳደር እና ልማት ዘርፍ ሃላፊ ም/ኮሚሽነር ጀነራል ይህደጎ ስዩም  በችግኝ ተከላው ወቅት እንደገለፁት ዓለማችንም ሆነ ሀገራችን እያስቸገረ ያለዉ የአየር ንብረት መዛባት ለማስተካከል በሚደረገዉ ጥረት የፖሊስ አባላቱ በየአመቱ እንደሚሳተፉ  በመግለፅ የዛሬዉ ልዩ የሚያደርገዉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሁለት መቶ ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ችግኞችን የተከለበት ቀን በመሆኑ የዚህ ተሳታፊ መሆናቸዉ እንዳስደሰታቸዉ ተናግረዋል፡፡ችግኝ መትከል ብቻ የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ የገለፁት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ  የአየር ንብረት መዛባትን መከላከል የሚቻለዉ ሁሉም  የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ ሲቻል ነዉ ብለዋል፡፡

         በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ፋሲል አሻግሬ   በበኩላቸዉ  የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ፕሮግራሙ  በሀገራችን  የተዛባዉን የአየር ንብረት በማስተካከል ንፁህ አካባቢ እንዲፈጠር የማድረግ አላማ ያለዉ ስለሆነ በአረንጓዴ ልማት ዘመቻዉ በመሳተፋቸዉ  ልዩ ደስታ እንደተሰማቸዉ ገልፀው ሰዎች ልጆቻቸዉ አድገዉ ለፍሬ እንዲበቁ እንደሚጓጉ ሁሉ የተተከሉት ችግኞች አድገዉ ጥላ ሆነዉ ሀገራችንን አረንጓዴ እንዲያደርጉ ሁሉም መንከባከብ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

        ማህበረሰቡ የተከላቸዉን ችግኞች በንቃት መጠበቅ እና በችግኞቹ ላይ አደጋ ሊያደርሱ በሚችሉ አካላት ዙሪያ ጥቆማ በመስጠት በህግ እንዲጠየቁ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡