የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥቅምት 12/2012 ዓ/ም

          በዛሬው ዕለት ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ መግቢያ ጀሞና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞችና አካባቢዎች የመንገድ መዘጋት ምልክቶችና ተግባራት ታይተዋል፡፡የዚህ መንገድ መዘጋት መነሻ የሆነው ጉዳይ አቶ ጀዋር መሀመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ያስተላለፉት መልዕክት ስለነበር ነው፡፡ መልዕክቱ በዋናነት ‹‹ልታሠር ነው፤ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው› የሚል ሲሆን ይሁንና በመንግስትም በፖሊስም በኩል ምንም አይነት ዕርምጃ አልተወሰደባቸውም፡፡ በሙሉ ጤንነትና እንደወትሮው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

           ፖሊስ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሐገር የገቡ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች በሚኖሩበት እና በሚንቀሳቀሱበት አካባቢና ቦታ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግላቸው ቆይቷል፡፡ ሀገሪቷ ውስጥ ይንፀባረቁ የነበሩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየተፈቱ ሠላማዊ ሁኔታ እየተረጋገጠ በመምጣቱ እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሠላም ተንቀሳቅሰው መኖር የሚችሉ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የግል ጥበቃዎችን የማንሳት ስራ ሥንሠራ ቆይተናል፡፡ ለወደፊቱም ባለን  አሰራር ይህንን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ስለዚህ ግለሰቡ በፖሊስ ዕርምጃ ተወሰደብኝ ብለው ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ስለሆነ፡- ወጣቶች፤ ህብረተሰቡ፤ በየአካባቢው የምትገኙ የፀጥታ ሀይሎችና አመራሮች የተዘጉ መንገዶችን በማስከፈት ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ እንድታደርጉ አሳስባለሁ፡፡

         በመጨረሻም ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር እና በመቆጣጠር የተጀመሩት የሰላምና የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የየራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ከአደራ ጭምር ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!