የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከተቋቋመበት 1939 ዓ.ም ጀምሮ የፖሊስ መኮንኖችን እና ሙያተኞችን በማፍራት ለሀገሪቱ ፖሊስ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለፀ፡፡

              በአጫጭር አመራር እና ልዩ ልዩ ፖሊስ ኦፕሬሽን ስልጠና ማዕከል ከሚሰጡ የአመራር እና የሙያ ስልጠና አይነቶች መካከል ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተር የሚደረግ የማዕረግ ሽግግር የአመራር ማበልፀጊያ ስልጠና ይጠቀሳል፡፡ሰሞኑን መስፈርቱን አሟልተዉ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ገብተዉ የነበሩት 74 የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ፖሊስ መኮንኖች ለከፍተኛ አመራርነት አቅማቸዉን ሊያሳድግ የሚችል ትምህርት በመዉሰድ ተመርቀዋል፡፡ተመራቂዎቹ በቆይታቸዉ የትራንስፎርሜሽናል አመራር፣የሰብአዊ መብት አያያዝ እና የፖሊስ አመራር ሚና፣የፖሊስ ስነ-ምግባር እና የአመራር ሚና፣የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት አመራር እና ዉሳኔ አሰጣጥ፣ዴሞክራሲያዊ የግጭት አፈታት ዘዴ እንዲሁም የወንጀል መከላከል እና ወታደራዊ ስልጠናዎች መዉሰዳቸዉ ታዉቋል፡፡

              በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አና የኢትዮጽያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ መስፍን አበበ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት በሰጡት የስራ መመሪያ "ፖሊስነት ራሳችንን ለሰፊዉ ህዝባችን አሳልፈን የምንሰጥበት ሙያ ነዉ" ብለዋል፡፡ ተመራቂዎቹ በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ያገኙትን ትምህርት በፊት ከነበራቸዉ የስራ ልምድ ጋር በማጣጣም ከፍተኛ የስራ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ ከአደራ ጭምር  አስገንዝቧል ሲል መረጃዉን ያደረሰን በኢትዮጽያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የዉጭና ህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ነዉ፡፡